ክብሩ አሰፋ ተወልዶ ያደገው በጎንደር-ታች አርማችሆ ማሰሮ ደንብ ነው፡፡ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ክብሩ አሰፋ የጀግኖቹ አርበኞች አታለል አሰፋና ክፈተው አሰፋ ታናሽ ወንድም ነው፡፡
ጀግናው አርበኛ አታለል አሰፋ በ1994 ዓ.ም ወደ በረሃ ወጥቶ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የተቀላቀለ ሲሆን በወልቃይትና በአርማጭሆ ለባንዳው የህወሓት ሰራዊት የእግር እሳት በመሆን መውጫና መግቢያ ነስቶታል፡፡
አርበኛ አታለል አሰፋ ከልቡ አርበኛ ነበር፤ አርበኛ አታለል አሰፋ እጅግ ጀግና ተዋጊ ነበር፤ አርበኛ አታለል አሰፋ ብልህ የጦር መሪና ጀግና አዋጊ ነበር፡፡
አርበኛ አታለል አሰፋ በደሙ ከፃፋቸው አስደማሚ የአርበኝነት ታሪኮቹ፣ አስደናቂ ጀግንነቱና አንፀባራቂ ጀብዱው መካከል 150 አርበኞችን እየመራ ተከዜን ተሻግሮ ሚያዚያ 16 1998 ዓ.ም አርማጭሆ ጎደቤ ላይ ሰፍሮ ይገኝ በነበረው የህወሓት መራሹ መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ ጠንካራ ምት በማሳረፍ የጦር ሰፈሩን ሙሉ በሙሉ ደምስሶ በርካታ ቁጥር ያለው ወታደርና ዲሽቃ መማረኩ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
ጀግናው አርበኛ አታለል አሰፋ ለአራት ተከታታይ ቀናት የህወሓትን ሰራዊት አያራወጠ በእሳት አለንጋ በመግረፍ ሲፋለም ቆይቶ ሚያዚያ 20 1998 ዓ.ም ስናር ላይ በጀግንነት ወድቆ ውድና ክቡር ህይወቱን ለአገሩ ኢትዮጵያና ከጎኑ ተሰልፈው ይዋጉ ለነበሩት ለሚመራቸው 150 ጓዶቹ ሲል ከፈለ፡፡ ስሙ ከአርማጭሆ እስከ ወልቃይት ገኖ ተሰማ፤ ጀግንነቱ በስናርና ቋራ በረሃዎች አስተጋባ፤ የአርበኝነት ድምፁ በኤርትራ ምድረ በዳዎች ሁሉ ከፍ ብሎ አስገመገመ፡፡
አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ፤ እሱም ጀግና ብቻ እንዲፈጥር ከታደለው አርበኛ አታለል አሰፋ ከወጣበት ማህፀን የበቀለ ነው፡፡ አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከተመሰረተ ከአንድ ወር በኋላ በ1993 ዓ.ም በረሃ ወርዶ የአርበኝነቱን ጎራ ተቀላቀለ፡፡ አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ 1995 ዓ.ም....... ዘመን መሪቅ ላይ ከባንዳው ህወሓት ሰራዊት ጋር በጀግንነት ሲፋለም እጁ ላይ በጥይት ተመትቷል፡፡ በተጨማሪም 1996 ዓ.ም አቡጢር ላይ አርበኝነትን ሲያፋፍም በድጋሜ እግሩ ላይ ተመትቶ ቆሰለ፡፡ ከዚያም በሱዳን ምድር ተጠልሎ ቁስሉን በመታከም ላይ እያለ የሱዳን ደህንነቶችና የፀጥታ ኃይሎች ለህወሓት አሳልፈው ሰጡት፡፡
አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ ሰቆቃ እየተፈፀመበት በህወሓት ወህኒ ውስጥ ሲማቅቅ ለሦስት ዓመታት ከቆየ በኋላ በ2000 ዓ.ም ተመልሶ የአርበኝነት ትግሉን ተቀላቀለ፡፡ አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ በእስር ባሳለፋቸው ሦስት ዓመታት ውስጥም የፖለቲካ እስረኞችን በህቡ በማደራጀት የጎንደሩን ግዙፍ ባህታ ወህኒ ቤት የመስበር ሙከራ አድርጓል፡፡ አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ ዛሬም በአርበኝነት ሜዳ ላይ ይገኛል፡፡
ክብሩ አሰፋ የእነዚህ ጀግኖች አርበኞች ታናሽ ወንድም በመሆኑ የህወሓት የበቀል በትር ገላው ላይ አረፈ፡፡ ክብሩ አሰፋ ወንድሞቹ ባካሄዱትና እያካሄዱት በሚገኙት አርበኝነት ምክንያት በበቀል ስሜት ብቻ በተነሳሳው ህወሓት በ2002 ዓ.ም በደህንነት ታፍኖ ወደ ወህኒ ተወረወረ፡፡ ሰቅጣጭ የምርመራ ድርጊትም ተፈፀመበት፡፡ ቀጥሎም የፈጠራ ክስ ተመስርቶበት የይስሙላሁ የህወሓት ፍርድ ቤት የ18 ዓመት አስር በየነበት፡፡ በመጨረሻም ክብሩ አሰፋ 6 የመከራ ዓመታትን በአሰቃቂ እስር ካሳለፈበት ወህኒ በነሀሴ ወር 2007 ዓ.ም ድንገት ተሰወረ፡፡ ወላጆቹ "ልጃችን ክብሩ የት ደረሰ?" በማለት የጎንደሩን ባህታ ወህኒ ቤት ቢጠይቁ "ሸዋ ሮቢት ሂዱና ፈልጉት" የሚል ምላሽ ተሰጣቸው፡፡ ጀግኖች አርበኞች አታለል አሰፋንና ክፈተው አሰፋን ከአብራካቸው ከፍለው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት መሰዋእት ያቀረቡት የክብሩ አሰፋ ወላጆች ለሦስት ወራት ከአገር አገር እየተንከራተቱ የህወሓትን እስር ቤቶች አዳረሱ፡፡ ነገር ግን ልጃቸውን ክብሩን ፈፅሞ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡
ክብሩ አሰፋ በነሀሴ ወር 2007 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ በህወሓት ደህንነቶች ከታሰረበት አዳራሽ እንደተወሰደ አብረውት የነበሩት ታሳሪዎች መስክረዋል፡፡ ህወሓት ከደርግ የከፋ ረሻኝና በቀለኛ ሆኗል፡፡
ጀግናው አርበኛ አታለል አሰፋ ለኢትዮጵያ ነፃነት ስናር ላይ በጀግንነት ወደቀ፡፡ አርበኛ ታጋይ ክፈተው አሰፋ እሱም እንደ ወንድሙ ለአገሩ ነፃነት ህይወቱን ሊከፍል ጦር ሜዳ ውስጥ ይገኛል፡፡ ክብሩ አሰፋን ህወሓት የበቀል ጥሙን ለማርካት ሲል ብቻ በግፍ ረሸነው፡፡ እናት ያለሀኪም እርዳታ ብቻዋን አምጣ ወልዳ ፍዳዋን ከፍላ ያሳደገቻቸውን ሦስት ወንድልጆቿን በባንዳው ህወሓት አጣች፡፡
No comments:
Post a Comment