ኢሳት (ህዳር 14 ፣ 2008) በደቡብ ምዕራብ ቴፒ ከተማ የተቀሰቀሰውን አስተዳደራዊ አለመግባባት ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው መስፈሩ ተገለጠ። በከተማዋ ላይ የተነሳው የይገባኛል አስተዳደራዊ ጥያቄ ስምምነት ባለማግኘቱ በርካታ ሰዎች በተቃውሞ ጫካ መግባታቸውንና ድርጊቱ በከተማዋ ውጥረት ማንገሱን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከሚዛን ተፈሪ ወደ ቴፒ፣ ከሸሸንዳ ከተማ ወደ ቴፒ፣ ከሚሻ ከተማ ወደቴፒ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ታውቋል። በንግድ እንቅስቃሴዋ የምትታወቀው የቴፒ ከተማም ከወትሮ በተለየ መልኩ የስጋት ቀጠና ሆና መሰንበቷን የተከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በይፋ የተገለጸ የሰዓት እላፊ ገደብ ባይኖርም የከተማዋ ነዋሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድላቸው ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል። ቴፒ ከተማ የምትገኝበት የኪ ወረዳን ለማስተዳደር በሸኮ ብሄረሰብ ተወላጆችና በሸካ ብሄረሰብ ተወላጆች መካከል ፖለቲካዊ ጥያቄ መነሳቱንና ችግሩ እልባት አለማግኘቱን የከተማዋ አስተዳደር ይገልጻል። አስተዳደራዊ ጥያቄው መግባባትን ሊፈጥር ባለመቻሉም ተቃውሞ ያስነሱ በርካታ ሰዎች ጫካ ገብተው ኣንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን፣ በአካባቢው ሰፍሮ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት እነዚህን ሃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመቻ ከፍቶ እንደሚገኝ ታውቋል። ይሁንና ድርጊቱ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የተፈጠረው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄን እንደሚፈልግ የገለጹት ነዋሪዎች፣ የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ በተጠሩ መድረኮች አስተያየት የሰጡ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስረድተዋል። “በአደባባይ ሃሳብን መግለፅ በራስ እንደመፍረድ ይቆጠራል” ሲሉ ነዋሪዎቹ የችግሩን አሳሳቢነት ገልፀዋል። ከአመታት በፊት ጀምሮ በከተማዋ የአስተዳደራዊ ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸው ይታወሳል። ባለፈው አመት የቴፒ ወህኒ ቤትን የሰበሩ ታጣቂዎች የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ አራት ፖሊሶች በመግደል እስረኞቹን ይዘው ወደጫካ መግባታቸው ይታወሳል። የመንግስት ሃይሎች ከእነዚህ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ያደረጉት ሙከራ በድምፅ ተቀርጾ ለኢሳት መድረሱንና ይህም መዘገቡ አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment