Thursday, November 26, 2015

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ደግሞ በሰሜኑ ክፍል እንደልብ ከቦታ ቦታ መዘዋወር እጅግ በጣም ከባድ እየሆነ እንደመጣና ህዝቡ የመንቀሳቀስ ነፃነቱ ጠብመንጃ በታጠቁ የአገዛዙ ቡድኖች መገፈፉ ታወቀ፡፡


በእጅጉ እየተፋፋመ ከሚገኘው ባንዳነትን በአርበኝነት ከማስወገድ የመሳሪያ ትግል ጋር በተያያዘ ህወሓት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባሰማራቸው ክፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፌደራል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሰራዊት ጦር እንዲሁም ደህንነቶቹ በየጥቂት ኪሎ ሜትሮች የርቀት ልዩነት ቁጥር ስፍር የሌላቸው የፍተሻ ኬላዎችን በማቋቋም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ዜጎችን በብርበራ ስም ክፉኛ እያዋከበ፣ እያሸማቀቀና እያሸበረ ይገኛል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደርና ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ በሚወስዱ ጎዳናዎች ላይ የፍተሻ ኬላዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክረው የመንገደኞችን ሰብዓዊ መብት በረገጠ መልኩ ብርበራ፣ ማዋከብና ማሸብር እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ደሴ በተዘረጋው መስመር በቅርቡ በተጀመረው ከዚህቀደም ታይቶ የማያውቅና ያልተለመደ ጥብቅ ጥበቃ፣ ቁጥጥር፣ ብርበራና በጦር መሳሪያ ማስፈራራት ጋር በተያያዘ ህዝቡ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በአካባቢው ገብተዋል በሚል ግምት የትግል መንፈሱ እንደተነሳሳ እና የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ውስጥ ለውስጥ እየገለፀ እንደሆነ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ደግሞ ከጎንደር ሁመራና ከጎንደር መተማ በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ገደብ የሌለው ቁጥጥር ስለሚደረግ ህዝቡ በተለይም ደግሞ ወጣቶች ፈፅሞ በነፃነት መንቀሳቀስ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከጎንደር ወደ አርማጭሆ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴና መተማ ለስራ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች አርበኞች ግንቦት 7ን ለመቀላቀል እየተጓዛችሁ ነው በሚል በየቀኑ በገፍ እየታፈኑ ወደ ወህኒ በመጋዝ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የህወሓት አገዛዝ የተለያዩ ወንጀሎችን ራሱ በማቀነባበር ደጋፊዎቹ ያልሆኑ መንገደኞችንና አሽከርካሪዎችን ወንጀል ሲሰሩ እጅ ከፍንጅ እንደያዛቸው በማስመሰል በቁጥጥር ስር አውሎ በሃሰት እያሰራቸው ነው፡፡ የህወሓት ደህንነቶች ከጭልጋ ወደ ጯሂትና ደልጊ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚመላለሱ የህዝብ መጓጓዣ ሚኒባሶች ላይ የጦር መሳሪያዎችን በስውር እየጫኑ ማጥቃት የሚፈልጉትን ግለሰብ ጠብቀው አሳበው በቁጥጥር ስር እያዋሉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከቦታው እየደረሱን የሚገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሰሞኑ የህወሓት ደህንነቶች የሰሌዳ ቁጥር 11243 የሆነች ሚኒባስ ላይ ወደ አስር የሚጠጉ ክላሽን ኮቮችን በድብቅ በማስጫን ሚኒባሷን ከጭልጋ ደልጊና ጯሂት በሚወስደው መስመር ከምትገኘው ብሆና ላይ ጠብቀው በቁጥጥር ስር በማዋል ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሊበቀሉት በሚፈልጉት ሰው ላይ እርምጃ ወስደዋል፡፡
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)

No comments:

Post a Comment