Monday, November 9, 2015

እነ የሺዋስ ለሶስተኛ ጊዜ ባልተገኙበት ቀጠሮ ተሰጠባቸው በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር



እነ የሺዋስ ለሶስተኛ ጊዜ ባልተገኙበት ቀጠሮ ተሰጠባቸው
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ከተበየነላቸው በኋላ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባቸው ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ዛሬ ጥቅምት 29/2008 ዓ.ም ለሶስተኛ ጊዜ ባልቀረቡበት ለህዳር 6/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም፣ ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም እንዲሁም ዛሬ ጥቅምት 29/2008 ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው ለሶስተኛ ጊዜ በሌሉበት የተቀጠረባቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ሀምታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሽበሺና አብሯቸው ይገብኝ የተጠየቀበት አቶ አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡

ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃ ዝርዝር ከብይን ጋር ተያይዞ ባለመቅረቡ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ መርምሮ ለመወሰን ስላልቻለ፤ ይግባኝ ያስቀርባል አያስቀርባል የሚለውን ለመወሰን በእስር ፍርድ ቤቱ ያሉ ዝርዝር የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ተያይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ሲሆን በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ ማስረጃዎቼ ያላቸውን አያይዞ ቀርቧል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ ‹‹መረጃዎቹ ስላልተመረመሩ መርምሮ ይግባኝ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለውን ለመወሰን›› በሚል ለህዳር 6/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment