በጎንደር ወገራ ወረዳ የተራቡ የሰባት ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ለመርዳት የተመደበው ገንዘብ በቆሎ ገዝተው አንዲያከፋፍሉ ለችፋንዝ ነጋዴዎች ተላልፎ በመሰጠቱ የበቆሎ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ ረሃቡን እንዳባባሰው የረሃቡ ሰለባ የሆኑ ዜጎች የሰቆቃ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡
የጎንደር ወገራ ወረዳ 7 ቀበሌዎች ነዋሪ የሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ክፉኛ ተርቦ ወደ እልቂት እያመራ ይገኛል፡፡ የሀወሓት አገዛዝ የረሃቡን አደጋ ለመቀነስ እስካሁን የወሰደው እዚህ ግባ የሚባል እርምጃ የለም፡፡ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ሊጠቀምበት አቅዶ ተፍ ተፍ ሲል ከሚታየው የይስሙላህ እርዳታ በስተቀር
በወገራና ዳባት ወረዳዎች የዘጠኝ ቀበሌዎችን ረሃብተኛ ህዝብ ለመርዳት በጥቅምት ወር የቀረበው 10ሺህ ኩንታል በቆሎ በአግባቡ እንዳልተከፋፈለና 10 ቤተሰብ ላለው አባውራ 10 ኪሎ ግራም ብቻ በመሰጠቱ የረሃብተኞችን ነብስ ከሞት ለመታደግ በቂ እንዳልሆነ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ የረሃቡን አደጋ ከልብ ለመቀነስ ሳይሆን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ታስቦ ለተጀመረው እርዳታ የተመደበው ጥሬ ገንዘብ ለኪንፋዝ ነጋዴዎች በመሰጠቱና ነጋዴዎቹ በቆሎ እየገዙ እንዲያከፋፍሎ በመደረጉ የአንድ ኩንታል በቆሎ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ ከ300 ወደ 600 መቶ ብር አሻቅቧል፡፡ እንጨትም ሆነ ከሞት የተረፉ መንቋዳ ጥጆቻቸውን ሸጠው ወይንም በምግብ እጦት በራደው ጉልበታቸው የቀን ስራ ውለው በሚያገኗት አነስተኛ ሽልንግ 1 ጣሳ በቆሎ ገዝተው ማታ ማታ ወደ ቤታቸው በመግባት ንፍሮ እየቀቀሉ ለጊዜውም ቢሆን ነብሳቸውን እንኳን እንዳያቆዩ አገዛዙ እርዳታ አደርጋለሁ ብሎ የእህል ገበያው ላይ አለመረጋጋት እየፈጠረ የረሃቡን እልቂጥ እያፋጠነው እንደሚገኝ ተጎጅዎች የሰቆቃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ላይ ናቸው፡፡ በነጋዴዎች እየተሸመተ በጣት ለሚቆጠሩ ረሃብተኞች መከፋፈል የጀመረው በቆሎም ከአድሏዊነት የፀዳ እንዳልሆነ ረሃብተኞች ጨምረው ብሶታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጎንደር ወገራ ወረዳ ለሰባት ቀበሌዎች በረሃብ የተጎዱ ነዋሪዎች ዘይት በመከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን እሱም ቢሆን ከአድሏዊነትና ከሙስና የፀዳ ካለመሆኑ ባሻገር መጠኑ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ የትኛውንም ያህል የቤተሰብ ቁጥር ይኑረው ለአንድ አባውራ አራት የቡና ስኒ ብቻ እየታደለ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በጎንደር ወገራ ወረዳ በደረሰው አስከፊ ረሃብ እና አገዛዙ ለረሃቡ እየሰጠው የሚገኘው ምላሽ አደጋውን የሚያባብስ በመሆኑ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ረሃብተኞች ቀዬዎቻቸውን እየለቀቁ እግራቸው ወደመራቸው በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment